የኢትዮጵያ ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ከሁለት ዓመት በፊት ገደማ ጀምሮ እንደ አጀንዳ ይዞ በተለያዩ ሚዲያዎች ሲወራ ሰምተናል፣ አይተናል፣ አንብበናል፡፡ ኮሚሽኑ በተደጋጋሚ ቆጠራና ምዝገባ ከተጠናቀቀ በኋላ ለህዝብ ይፋ እንደሚሆን ቃል ገብቶ ነበር፡፡ ይሁንና ይኸው ከሁለት ዓመት በላይ በኋላም ምንም ጠብ ያለ ነገር የለም፡፡ የተሰማ ነገር የለም፡፡ 2005ም ሊያልቅ ነው፤ መስከረም ሊጠባ ነው፡፡ ሲጀመር እኛ ተቆጥሮ ይነገረን አላልንም፤ ከተባለ በኋላ ግን አፋችንን ከፍተን ስንጠብቅ ነበር፡፡ ነው ወይስ ተቆጥሮ አላልቅ አለ፤ የተበታተነ ንብረት ካለ ምናልባት፡፡ ባለስልጣኖቻችን እንደሆኑ እንግዲህ በPay roll ነው የሚከፈላቸው፡፡ እንበልና አንድ ባለስልጣን ከ83 ዓ.ም ጀምሮ ስልጣን ላይ ቢሆንና እስከ 2005 ዓ.ም በየወሩ 4,000 የኢትዮጵያ ብር የተጣራ ደሞዝ ቢከፈለው ሂሳቡ፡-
4,000ብር X 22ዓመት X 12ወራት = 1,056,000 ብር ይሆናል፡፡
ይህን የሚያጠራቅመው ደሞዙን ለምንም ነገር ባያውለው ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም ባለስልጣኖቻችን መቼም ማክያቶ ለመጠጣት ጊዜ የላቸውማ፡፡ ለነገሩማ እንደሚወራው ከሆነ እኮ የሚከፈላቸው ደሞዝ አነስተኛ ቢሆንም፤ ብዙ ጠያቂ አላቸው ነው የሚባለው፤ ልክ ሰሞኑን እንደተስተዋለው የጉምሩክ ባለስልጣና ኃላፊዎች በተግባር እንዳሳዩት ማለት ነው፡፡ ልክ በጃንሆይ ጊዜ ሲደረግ እንደነበረው ማለት ነው፡፡ አንድ ጉዳይ ለማስፈፀም በግ እየጎተቱ የሚሄዱበት ጊዜ ነበር፤ አሁን አድጎ በውጭ ምንዛሬ፣ በህንፃዎች፣ በፋብሪካዎች፣ ወ.ዘ.ተ… ሆኗል፤ ምክንያቱስ ከአገራችን እድገት አንፃር ነዋ፡፡ በነገራችን ላይ ሙስና ባይኖር እኮ አዲስ አበባችን እነዚህን በመሳሰሉ ረዣዥም ህንፃዎች አትሽቆጠቆጥም ነበር፤ ጠቀሜታውን ከዚህ አንፃር እንቃኘው፡፡
ወደ ዋናው ጉዳይ ልመልሳችሁና ይህች ተቆጥራ የምታልቅ የPay roll ገንዘብ እንዴት የህን ያህል ጊዜ እንደፈጀች ሊገባኝ አልቻለም፡፡ ቢሆንም በቀጣዩ ምርጫም ጊዜ ቢሆን እኛ እንዲነገረን እንፈልጋለን፡፡ በደሞዙ እየተሸማቀቀ፣ የቤት ኪራይ ከደሞዝ በላይ የሚከፍል፣ የሚበላው፣ የሚጎርሰው፣ የሚለብሰው፣ የሚጠጣው ያጣ የመንግስት ሰራተኛ (Civil Servant) ተብሎ ግብዳ ስም ወጥቶለት የሚኖር ስንቱ ነው መሰላችሁ፤ ብቻ “ቤት ይቁጠረው” ወይም “ሆድ ይፍጀው” ብለን እንለፈው እንጂ፡፡ “ሁሉን ሲናገሩት ሆድ ባዶ ይቀራል” ነው ያለችው ዘፋኟ፡፡ “Civil Servant” የሚለው ቃል “የህዝብ አገልጋይ” የሚል አቻ ትርጓሜ ያለው ሲሆን፤ የሚሰጠው ደሞዝና ክብር ግን በድሮ ጊዜ “ባሪያ” ተብለው እየተገረፉ ሲሰሩ ከነበሩት በጣም የወረደ ነው፤ ለዛውም የዛን ጊዜ ባሪያዎች የሚበሉት እስከሚጠግቡ ነው፤ ለሚኖሩበት ቤት አይጨነቁም፡፡ እና ምን ለማለት ፈልጌ ነው የህዝብ አገልጋዩ ተሰቃይቶ እንዲኖር የተፈረደበት ይመስል፤ እንዲሁ ቀን ያልፋል እያለ እየተንፏቀቀ እየኖረ ይገኛል፡፡ ይህ ሁሉ እሮሮ የሁሉም የመንግስት ሰራተኛ ነው፡፡ ኑሮ ሲወደድ፣ የእቃ ዋጋ ሲንር፣ የሚጠቀመው ነጋዴውና የግል ተቀጣሪው ነው፡፡ እነሰሱ አያግኙ ማለቴ አይደለም፡፡ ነጋዴዎች የገበያ ላይ ዋጋ ሲጨምሩ ለመንግስት ሰራተኛው ትንሽ ድጎማ ቢጤ ታስፈልጋለች ማለቴ ነው፡፡ ዋናውን ርዕሴን ትቼ ወደ እሮሮ ገባሁ እኮ፤ ይቅርታ ይህ ነገር ስለሚከነክነኝ ነው፡፡ ብዙ ጓደኞቼ የመንግስት ሰራተኛ በመሆናቸው የማየውን ነው ያወራሁት፡፡ ስለሆነም በመጨረሻ የባለስልጣኖቻችን ሀብት ተቆጥሮ፣ ሰባራ ሳንቲም ሳይቀር፣ እንዲነገረን እንፈልጋለን፡፡