ሪፖርተር ጋዜጣ ላይ ደመቀ ከበደ የተሰኘ ገጣሚ ያቀረባት ግጥም ስለመሰጠችኝ ላካፍላችሁ ወደድኩ፡፡
==========
እኒያ የኔ ሰዎች
ከወንዝ ወዲያ ማዶ - በሩቅ የማያቸው
‹‹አትመጡም ወይ›› ብዬ - ለምጠይቃቸው
ከአፍ የሚወጣቸው
አንድ ነው ቃላቸው
‹‹እንጃ›› ነው መልሳቸው፤
እኒህም የኔዎች
አጠገቤ ያሉ - ሰርክ የማገኛቸው
ያልገባኝን ጉዳይ - ሁሌ ሳዋያቸው
ምንም ሳይዛነፍ - ‹‹እንጃ›› ነው መልሳቸው፤
‹‹ ከ‹እንጃ› ምሶሶና - ከ‹እንጃ› ባላ፣ ማገር
በ‹እንጃ› ባይ አናፂ - በታነፀች አገር
ከ‹እንጃ› ማለት በቀር
ለጥያቄ ሁሉ - ምላሽም አልነበር?››
ብየ እጠይቃለሁ
ብየ እጨነቃለሁ
ከጥያቄ ጋን ውስጥ - ጥያቄ እጠልቃለሁ፤
የምሬን እኮ ነው፤
‹‹ከ‹እንጃ› ባይ አገሬ
ከ‹እንጃ› የተሻለ - የአገር ምላሽ ባገኝ
‹ለምን?› አስረግዞ - ‹ለምን?› የወለደው - የሚያንገበግበኝ
ምላሽ ያጣሁለት - ጥያቄ ነበረኝ፤››
ብዬ እተክዛለሁ
ከጥያቄዬ ላይ - ጥያቄ እመዛለሁ፤
‹‹ማንን ነው ማዋየው - ወይ የማማክረው
የልቤ ጥያቄ - ልቤን ተረተረው፤››
እያልኩ አስባለሁ - ድንገት እነጉዳለሁ
ከጥያቄዬ ጋር - እወጣ እወርዳለሁ፤
ቢጨንቀኝ ጊዜ እንጂ፤
በ‹‹እንጃ›› አገር ተፈጥሮ - በ‹‹እንጃ›› ምላሽ አድጎ - ‹‹እንጃ›› ሲል ለኖረ
ከ‹‹እንጃ›› ማለት በቀር - ከ‹‹እንጃ›› የተሻለ - መልስም አልነበረ፤
ሀቅ ይኸውላችሁ፤
በዚች አገሬና - በዚች አገራችሁ
‹‹ምን ይበጀን ይሆን›› - ለሚል ጥያቄዬ - ለሚል ጥያቄያችሁ
‹‹እንጃ›› ነው ምላሹ - ‹‹እንጃልህ፣እንጃልሽ›› - ወይም ‹‹እንጃላችሁ››፡፡
© ደመቀ ከበደ