Monday, September 8, 2014

የጳጉሜ ወር ጣጣ

ጳጉሜ እንደምናውቀው የሀገራችን ኩራት የሆነች፣ “13 months of sunshine” እየተባልን በዓለም አቀፍ ደረጃ የምንኩራራባት፣ አምስትና ስድስት ቀናት እየሆነች የምታደናግረን፣ አንድ ወር ትሞላለች ብለን ድርቅ ብለን ራሳችን ላይ የለጠፍናት ሚጢጢ ወር ናት፡፡ በእርግጥ ከፈረንጆቹ የፀሃይ ዑደት አቆጣጠር እና ከአረቦቹ የጨረቃ ዑደት አቆጣጠር ዘዴዎች በእጅጉ የተለየ የአቆጣጠር ዘይቤ አለን፤ በኢትዮጵያ ውስጥ፡፡ በጣም የሚገርመው ደግሞ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ አራት ወቅቶችን በጠበቀ መልኩ ምንም ሳይዛነፉ እንዲታዩ የሚያደርግ የቀን አቆጣጠር ነው ያለን፡፡ ይህች ወር ግን ተቀጣሪዎች (የመንግስት) ምንም ሳያገኙ ወዛቸውን ሰጥተው ያለደመ-ወዝ በነፃ ህዝቡን የሚያገለግሉባት ወር ነች፡፡ ስለዚህ ይህች ወር ለሀገራችን በነፃ የሆነ ነገር የምናበረክትባት ድንቅ ወር ነች፡፡ በእርግጥ ወር አትባልም ሳምንት እንበል፡፡ ምክንያቱም ለክፍያ ሲሆን ሳምንት፤ ለዘመን አቆጣጠር ሲሆን ግን ወር ነቻ፡፡
ታዲያ በዚህች ጳጉሜ ወር የተነሳ ሰሞኑን ከቤት አከራዬ ጋር እንደጭቅጭቅ ነገር አጋጥሞኛል፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው፤ ብዙ ጊዜ ተከራይቼ ስኖር የጳጉሜ ወርን ያስከፈለኝ የለም፡፡ ይህችኛዋ ወይዘሮ ግን “የጳጉሜ ወር ኪራይ ትከፍላለህ” አሉኝ፡፡ እኔንስ ማን ችሎኝ፡፡ “እኔ የህዝብ አገልጋይ የመንግስት ሰራተኛ ነኝ፤ ይህችን ወር በነፃ እንደማገለግል አያውቁም ወይ” ስላቸው “እኔ ስለሱ የሚያገባኝ ነገር የለም፤ አኔ የማውቀው አንድ ወር 30 ቀን እንደሆነ ነው፤ ይህች 5 ቀን ደግሞ ተጨማሪ ነች፤ ስለዚህ ትከፍላለህ፤ ትከፍላለህ” አሉኝ፡፡ እኔም ማምረራቸውን ሳውቅ መለስ አልኩና “እኔ የማውቀው በዓመት ውስጥ 12 ወራት እንዳሉ ነው፡፡” አልኩ:: የተማርነውም እንደዚህ ነው፡፡ ግን ጳጉሜን እኮ ከአሁን በፊት እንደምኮራባት ለብዙ ሰዎች አውርቻለሁ፡፡ “ከዚህም በተጨማሪ ፈረንጆች ጋር 12 ወር ነው ያለው፡፡ አንድ ወር 31፣ 29፣ 30 ወይም 28 ቀናት ሊኖሩት ይችላሉ፡፡” ስላቸው “የኔ ልጅ እኔ ኢትዮጵያዊ ነኝ፤ የፈረንጅ አቆጣጠር እዚህ ምን አመጣው፡፡” ተባልኩ፡፡
አላዋጣኝ ሲል የተማፅኖ ዓይነት ትምህርት ልሰጣቸው ፈልጌ “የዜግነት ግዴታዎን በዓመት ውስጥ ለ5 ቀናት በነፃ ቢያኖሩ ምኑ ላይ ነው ነውሩ፡፡” ልላቸው አሰብኩና ተውኩት፡፡ ምክንያቱም የመብራት፣ የውሃ፣ የሽንት ቤት በነፃ የሚገኝ ይመስልሃል ብለው እንደሚመልሱልኝ አውቃለሁ፡፡ መቼም ይህች የአገልግሎት ክፍያ በወር ከ10 ብር ላትበልጥ ነገር የአዲስ አበባ አከራዮችን እንዴት እንደሚያንጨረጭራቸው አይገባኝም፡፡ እነሱ ለጋገሩበት ምጣድ ተከራዩን ማስከፈል ይፈልጋሉ፡፡
እና ምን ለማለት ፈልጌ ነው የሚመለከተው አካል ወይ እንደኔ ዓይነቱ ለጳጉሜ ወር ክፍያ እንዲያገኝ አለበለዚያም የቤት አከራዮች እኩል የዜግነት ግዴታቸውን እንዲወጡ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ ምክንያቱም ጳጉሜ የዓመቱ “ቫት” ነች፡፡ የሚከነክነኝን ነገር ማንሳት ስለፈለኩ ነው እንጂ ጳጉሜማ አንዷ የቱሪስት መስህብ እኮ ናት፡፡


Ethiopian Overlooked and Underutilized Sector - Agriculture

Agriculture is the prominent sector of Ethiopia which millions of lives depend on for centuries. The share still stands high compared ...