ለመጀመር ለጠቅላላ እውቀታችሁ
ያህል የላፕቶፕ ዋጋን አነሳለሁ፡፡ ትንሽ ተብሎ የሚጠራው ዋጋ 12 ሺህ ብር ነው፡፡ ታዲያ በዚህ መልኩ አድርጎ የቴክኖሎጂ ርቀ’ት እንዴት ይመጣል እንዲያውም ድቀት እንጂ፡፡ በአሁኑ ወቅት እንደሚታዬው አንዲት ሀገር ለማደግና
ለመበልፀግ በሃይ-ቴክ ፋሲሊቲዎች፣ ሶፍትዎሮችና በተለያዩ ቴክኖሎጂዎች መታገዝ አለባት፡፡ ይህ የሚሆነው ዝም ብሎ አይደለም፡፡ የኮምፒዩተር
ዋጋ እንደዚህ በተሰቀለበት ጊዜ እንዴት ተብሎ ነው ስለ ብልፅና የሚታሰበው፡፡ ከትንሹ እንጀምር የወረቀት ስራ ለመስራት እንኳን
ኮምፒዩተር ቤት ሄደን ነው የምናፅፈው፤ የፈለገ ምስጢር እንኳን ቢሆን፡፡ ይህ ለምን ይሆናል? ኮምፒዩተር ይዘው የምናያቸው ቀበጥ
የሀብታም ልጆች ናቸው፡፡ በእርግጥ ከሀብታም ልጆች በጣም ጎበዞች አሉ፡፡ ዓላማቸውን ተረድተው ግብ ለመምታት የሚጥሩ፡፡ አብዛኛዎቹ
ግን ሙዚቃ ከመስማትና ፊልም ከመጫንና ከማውረድ ውጪ ምንም ሲያደርጉበት አይታይም፡፡ በጣም የሚገርመው ደግሞ በተለይ በመንግስት
መስሪያ ቤቶች ውስጥ ላፕቶፕ መያዝ የስልጣን ደረጃን ለመግለፅ የተቀመጠ መስፈርት ይመስል ምንም ዓይነት መሰረታዊ የኮምፒዩተር እውቀት
የሌላቸው ባለስልጣናት ባዶ ኮምፒዩተር ሲዞሩ ማየት የተለመደ ነው፡፡ እና ምን ለማለት ፈልጌ ነው፡፡ ዋጋው ተመጣጣኝ ቢሆንና በእያንዳንዱ
ሰው ቤት ውስጥ ቢገባ ከቴክኖሎጂ ጋር የተያያዙ የፈጠራ ስራዎቸ እርግጠኛ ሆኜ የምነግራችሁ ቢያንስ አሁን ካሉበት ከ200 ፐርሰንት
በላይ ይጨምራሉ፡፡ ይህም የሚሆነው እንዴት ነው? የመንግስት የቤት ስራ ነው፡፡ በኤሌክትሮኒክስ ላይ በተለይም በኮምፒዩተሮች ላይ
የጣለውን እጥፍ የግብር ክፍያ ማንሳት ወይም መቀነስ አለበት፡፡ ይህ ካልሆነ ግን ይህች ሀገር ብዙ እርምጃ ወደፊት አትሸጋገርም፡፡
ለምሳሌ ልማታዊ ባለሀብቶች ናቸው ለሚባሉ ባለሀብቶች ግን ልማታዊ ላልሆኑ ከቀረጥ ነፃ ተፈቅዶላቸው ያልረባ ዕቃ አስገብተው ለሥራ
ሳያውሉት መርካቶ የሚሸጡ ስንቶች ናቸው፡፡ ‘ብቻ ሆድ ይፍጀው’ ነው ‘ቤት ይቁጠረው’ የሚባለው፡፡ ይህን በመረጃ ለማስደገፍ ባልችልም
እንዲሁ ግን ይታወቃል፡፡ ወይም ቀረጥ መቀነስ ካልቻለ መንግስት እራሱ ጣልቃ ገብቶ በተመጣጣኝ ዋጋ ከአቅራቢዎች ጋር ተስማምቶ የሚያስመጣበትን
አሰራር ቢቀይስ ይሻላል፡፡ ይህም ካልተቻለ ደግሞ ልክ ቶርች ላይት አፕሊኬሽን ያላቸውን ሞባይሎች አገር ውስጥ መገጣጠም እንደተጀመረው
ለትላልቅ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ፈቃድ ሰጥቶ ሀገር ውስጥ እንዲሰሩ ማድረግ ጥሩ አማራጭ ነው፡፡
ከላይ ከተጠቀሱት አማራጮቹ የማንጠቀም
ከሆነ ግን ወደፊታችን ምን እንደሚሆን አይታወቅም፡፡ ከቴክኖሎጂ ጋር አብረን መራመድ ብንችል ጥሩ ነው፡፡ በሀገራችን የሚቀረፁ ፊልሞችን
ጥራት ብንመለከት እንኳን በ20ኛው ክፍለ ዘመን የተቀረፁ የቻርሊ ቻፕሊን ፊልሞችን እንኳን አያክሉም፡፡ ይህም የሚያመለክተው የሚቀርፁበት
ካሜራ ልክ በባለ 2 ሜጋ ፒክስል ሞባይላችን እንደምንቀርጽበት አይነት ነው ማለት ነው፡፡ በአሁኑ ሰዓት HD (High Definition) የሚባሉ ካሜራዎችን ነው ዓለም ሁሉ የሚጠቀመው፡፡ እስካሁን ‘ጤዛ’
የተሰኘው የፕሮፌሰር ኃይለገሪማ ፊልም ብቻ ነው ጥርት ብሎ መስጦኝ ያዬሁት፡፡ ፊልም እኮ ታሪካዊ ፍሰቱ ብቻ አይደለም የሚመስጠው፤
አቀራረፁም ጭምር ነው፡፡
ለማንኛውም ይህን ሁሉ የምቀባጥረው
ስለፊልም ምንነት ለመናገር አይደለም፡፡ ወደ ዋናው ቁም ነገሬ ስገባ ሀገሪቷ ከቴክኖሎጂ ፈጠራዎች ተጠቅማ በፍጥነት ማደግ እንድትችል
የቴክኖሎጂ ግብዓቶች ያስፈልጓታል፡፡ ከድንጋይ ተጠርቦ፣ ከእንጨት ተቀጣጥሎ የሚሰራበት የድንጋይ ዘመን ላይ አይደለም ያለነው፡፡
እነዚህ ፈጠራዎች የአኗኗር ዘይቤያችንን በመጠኑ ቢያሻሽሉትም ሙሉ በሙሉና ዘላቂ በሆነ መልኩ አይቀይሩትም፡፡ ዓለም እኮ ቆሞ አይጠብቀንም፡፡
እኛ ደግሞ በ2020 መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሃገራት ተርታ አገራችንን እናሰልፋለን ብለን የምናወራው እኮ መቼም በሩጫና በእግር ኳስ
አይደለም፡፡ ይልቁንም የህብረተሰቡን የኑሮ ደረጃ ፈርጀ-ሰፊ በሆነ መልኩ ለማሳደግ ነው፡፡
እናም አኔ የምለው አንድ በሉ
ነው፡፡ ሌላማ ምንስ ልናገር፡፡ ይህ የኔ ድምፅ ብቻ አይደለም፡፡ ይልቁንም በኮምፒዩተር እጥረትና ናፍቆት የሚቃጠሉ የኔ ብጤዎችም
ጭምር እንጂ፡፡