አዲስ አበባ፤ የውጭ እንግዶች መቀበያ፤ በእርግጥ እንግዶችን ማስተናገድ ባህላችን ቢሆንም፤
አንዳንዴ ግን ከገደብ ያልፋል፡፡ ይህን ለማለት ያበቃኝ ምን መሰላችሁ፡፡ ሁልጊዜ የአፍሪካ ህብረት ስብሰባ፣ የተለያዩ ሀገራት መሪዎች
ስብሰባ፣ የሚኒስትሮች ስብሰባ፣ … ስብሰባ፣ በአጠቃላይ የጠቃሚ ሰዎች (VIP) ስብሰባ ሲኖር፤ በሚያጋጥመው የመንገድ መዘጋጋት ምክንያት በሃገሮው ሰዎች ላይ ይህ ነው
የማይባል የጊዜና የኢኮኖሚ ቀውስ ያስከትላል፡፡ ታክሲ ለማግኘት አበሳ፣ ከተገኘ በኋላም ቀስ እያለ እየተንፏቀቀ በታሰበው ጊዜ ለመድረስ
አይቻልም፡፡ ይህንን የማይረዱ ሰዎች አሉ፡፡ የቢሮ አለቃዎች አርፍደህ ስትገባ በአፍሪካ ህብረት ስብሰባ ምክንያት ነው ብትላቸው
አይሰሙህም፡፡ እንዲያውም ይባስ ብሎ ከወር ደሞዝህ ይቆረጣል፡፡ ከዚህ አንፃር የአፍሪካ ህብረት መሪዎች የደሞዛችን ፀር ናቸው ማለት
ይቻላል፡፡ ተማሪ ከሆንክና የፈተና ጊዜ ከሆነ፤ ሰዓት አሳልፈሃል ተብሎ ፈተና መቀመጥ አይችልም፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ የትምህርት
ፀር ስብሰባ ሆነ ማለት ነው፡፡ መች ይሄ ብቻ ለምሳሌ የነፍስ አድን ጥሪ የደረሰው የኔ ብጤ ባተሌ በታሰበው ጊዜ ደርሶ ቤተሰቡን
ለማሳከም ጉዞ ቢጀምር የሚደርሰው ለቀብሩ ነው ማለት ነው፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ፀሃፊው እንዳለው ስብሰባዎች ሲካሄዱ ብቻ የሚከፈቱ የቦሌ፣ የሜክሲኮና ሌሎች
የማላውቃቸው በጣት የሚቆጠሩ ፋውንቴኖች አሉ፡፡ ይህም የሆነው ለውጭ ሰው ስለምናጎበድድ ነው እንጅ መቼም የውሃው ቁልፍ መሪዎቹ
ኪስ ውስጥ ስለሚቀመጥ አይደለም፡፡ ያገሬ ሰው ፋውንቴን ማየት አያዝናናውም ወይ?
እንዲያውም
አብዛኛው ሰው እግረኛ ስለሆነ ከኔ ጀምሮ ማለቴ ነው፡፡ መቼም ፋውንቴን ሲመለከት ዘሎ ገብቶ ሻወር ልውሰድ የሚል እንደማይኖር ሁላችንም
እናውቀዋለን፡፡ ምክንያቱስ የሀገሬ ሰው ለባህሉና ለወጉ ነው የሚቆመው፤ ማነው በአደባባይ ልብሱን አውልቆ ሻወር የሚወስደው፤ ይልቅስ
ልብሱን አውልቆ ሽንቱን መሽናት ነው የሚቀናው፡፡ ይህንም ለማፅዳት ቢሆን ፋውንቴን ጠቃሚ ነው፡፡ መቼም ሃገራችን በውሃ እጦት አትታማም፡፡
አባይ አለ፤ አዋሽ አለ በየቦታው እየተጠማዘዘ እያጠጣ ጥም የሚቆርጥ፤ ኦሞ አለ፤ ባህርስ ብንል፤ ሃይቅስ ብንል፡፡ በእውነት በእውነት
ምን የሌለን ነገር አለ፤ የሌለው ውቅያኖስ ብቻ እኮ ነው፡፡
እንዲያውም ሀገሪቷ ዝም ብላ በፀጋ የተሞላች እኮ ናት፡፡ እንዲያውም ኢትዮጵያ ቅፅል ስሟ እኮ “የምስራቅ አፍሪካ የውሃ ማማ” ነው የምትባለው፡፡ ታዲያ ምን
ያደርጋል አለን እያልን ከማውራት ውጭ ስንጠቀምበት አይታይ፡፡
ለማንኛውም ስለውሃ አብዝቼ መናገሬ
እያለን እንደሌለን ለምን እንሆናለን፤ ለኛ ያልፈሰሰ ፋውንቴን የውጭ ባዕድ ሀገር ሰዎች ሲመጡ ብቻ ለምን ይከፈታል ለማለት ያህል
ነው፡፡ ለነገሩማ እኛ ኢትዮጵያውያን ስንባል በአዘቦት ቀን ሽሮ ስንከተክት እየከረምን የበዓል ቀን ሲመጣ አይደል ስጋን ጨምሮ ጥሩ
ጥሩ ነገር የምንበላው፤ ከዚህስ ተያይዞ አይደለ ወይ የሽንኩርት፣ የቲማቲም፣ የቃሪያ፣ እና ወዘተ… ዋጋ የሚጨምረው፡፡ ይቅርታ የጠቀስኳቸው
ምሳሌያዊ ምርቶች እኔ የምጠቀምባቸው ናቸው እንጂ የሌላውን አላውቅም፡፡ ፋውንቴን የሚከፈተውና መንገድ የሚዘጋው ለውጭ ሀገር ሰዎች
ከሆነ ሀገራችን ውስጥ ያሉ ስለሀገራችን ብዙ የሚያውቁ፣ የሚፅፉ፣ የተማሩ፣ ፕሮፌሰሮች፣ ዶክተሮች እንዲሁም በዚህች ዓለም ላይ ብዙ
ዝና ያላቸው ሰዎች ከተማችንን ከመመላለስም አልፎ ይኖሩባታል እኮ፡፡ እንዲያውም መሪዎች መጥተው ቤተ-መንግስትን ብቻ ነው አተኩረው
ማየት የሚፈልጉት፡፡ ምክንያቱም የቤተ-መንግስት አሰራር ጥበብን ከኢትዮጵያ ኮርጀው የራሳቸውን አፍርሰው ለመገንባት ስለሚፈልጉ፡፡
ለማንኛውም የዚህች ከተማ ጣጣ
በዚህ ብቻ የሚያበቃ አይደለም፡፡ እንዲያውም የተባ አንደበተኛ አለመሆኔ ነው እንጅ ስለዚህ ጉድ ለመፃፍ ቀለም አይነጥፍም ነበር፡፡
የእኛ ሀገር መሪዎች አሜሪካን ሀገር ቢሄዱ እንዴት ተብሎ ነው መንገድ የሚዘጋው፡፡ እንዲያውም ሴኩሪቲ ራሱ የሚመደብ አይመስለኝም፤
ግን አሜሪካ ሄጄ ስለማላውቅ ግምቴ ሊሳሳት ይችላል፡፡ የእኛ ሀገር ሰው ምንም ተንኮል አይሰራም፡፡ ለዚህም ማሳያው የሻእቢያና የአልሸባብ
ሽብር ሳይፈጠር እንዲደረስበት የሚያደርገው ህዝቡ ነው፡፡ እንግዲያማ የሀገራችን ደህንነት በየትኛው መሳሪያ ተጠቅሞ ነው እንደዚህ
የተቀነባበረ ዘመቻ ላይ ሊደርስበት የሚችለው፡፡ እንዲያውም አንዳንዴ የውጭ መሪዎች ገና ከአገራቸው ለአውሮፕላን ቡክ ሳያደርጉ ጀምሮ
መንገዱ ክፍት ይደረግላቸዋል፤ ለእኛ ግን ተዘጋግቶ ማለት ነው፡፡ ግን እኮ መንገዱ ለኛም ክፍት ቢደረግ እነሱን ከፊት አድርገን
እኛ ደግሞ ከኋላ ሆነን እያጨበጨብን እስ ቤተ-መንግስት እንሸኛቸው ነበር፡፡ ነገር ግን ብዙዎቹ የአፍሪካ መሪዎች በራሳቸው ስለማይተማመኑና
በሚስታቸውም ስለማይታመኑ መክተሚያቸው አዲስ አበባን በንቃት ይከትሙባታል፡፡
በአጠቃላይ የሰው ወርቅ አያደምቅ
ቢያደምቅም ለሞኝ ሰው ነው፤ ልክ መቼ ነው? የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ባሌስትራውን
ወርቅ ቀብተው እንዳታለሉት ማለት ነው፡፡ ብለን እንጨርሰውና ስብሰባ ቢቀነስ ጥሩ ነው፤ ስብሰባ ቢኖርም ህብረተሰቡን በማይጎዳ መልኩ
ቢሆን ጥሩ ነው፡፡ ለማንኛውም ይህ ሁሉ እሮሮ ሰሚ የሚያገኝ ከሆነ እሰየው፤ የማያገኝም ከሆነ እንዲያ እንደ ብሶት ይቀመጥና የወደፊታችንን
እንዲያሳምረው ፀሎትና ዱዓ ማድረግ ሳይሻል አይቀርም፡፡
No comments:
Post a Comment