“አዲስ አበባ፣
ዳርዳሯ አበባ፣
ውስጧ ሌባ፡፡”
የተባለላት አዲስ አበባ፤ ዋና ከተማ የሆነችበትን ጊዜ ለመቁጠር ወደኋላ አፄ ሚኒልክ የነገሱበትን ጊዜ ማስላት ያስፈልጋል፡፡ የዛን ጊዜ እቴጌ ጣይቱ እንጦጦ ላይ ሆነው ቁልቁል ሲመለከቱ ደስ አለቻቸውና “አዲስ አበባ” ብለው ሰይመው መኖሪያቸውን ወደዚህች ከተማ አዛወሩ፡፡ እነሆ ከዛን ጊዜ ጀምሮ አዲስ አበባ ቀስ በቀስ በእድገት ጎዳና ላይ ትገኛለች፡፡ ፎቅ መሰራት የተጀመረው በቅርብ ጊዜ ቢሆንም፡፡ ያን ሁሉ አልፋ አሁን ከተማዋ የፎቆች ውድድር የሚካሄድባት ይመስላል፡፡ ከወር በኋላ ቆይተህ የሆነ ሰፈር ብትሄድ አዳዲስ ፎቆች በቅለው ነው የምታገኘው፤ መንገድ የተሳሳትክ እስከሚመስልህ ድረስ ማለት ነው፡፡ እና አብዛኛዎቹን ፎቆች የሚያመሳስላቸው አንድ እውነታ አለ፤ ይኸውም የመስታውት ብዛት ነው፡፡ ፎቅ ያለመስታውት የማይሰራ ይመስል፡፡ ባለቤቶቹም የሚፈልጉት፣ አርክቴክቸሮቹም ዲዛይን የሚያደርጉት ተመሳሳይ ነገር፤ መስታውት በመስታውት የሆነ ቤት ነው፡፡ እኔምለው መስታውት እርካሽ ነው እንዴ? ከብሎኬት ጋር ሲነፃፀር፡፡ ለማንኛውም ይህን ስሌት ለመሃንዲሶች እንተወውና እንለፍ፡፡ ይህ የመስታውት ብዛት ከተማዋን ምድረ-በዳ እያደረጋት ነው፡፡ ምን ለማለት ፈልጌ ነው የመስታውቱ ነፀብራቅ ፊት ላይ ሲያርፍ ያቃጥላል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ እርግጠኛ ነኝ እስካሁን የዓይን ብሌኑ የተቃጠለ ሰው ይኖራል፡፡ ቤት ይቁጠረው ብለን እንተወው እንጂ፡፡ የመስታውት በረሃ ዋጠን እኮ ምን ይሻላል ትላላችሁ? ለዚህ ማስተማሪያ የሚሆን ማንኛውንም ፎቅ የሚያስንቅ ያየሁት ፒያሳ ላይ ያለው “እናት ህንፃ” ብቻ ነው፡፡ ሌሎቹ ሁሉም አንድ መሃንዲስ ዲዛይናቸውን የሰራቸው ይመስል ተመሳሳይ ናቸው፡፡ እኔምለው ዲዛይን ያለመስታውት አይቻልም አያምርም ያለው ማነው? ለማንኛውም መንግስትም የድርሻውን ቢወጣና ዓይናችን ከመጥፋቱ በፊት መፍትሄ ቢያፈላልግ፤ ባለሙያዎቹም ሙያቸውን የሚያሳድግ ነገር ቢሰሩ መልካም ነው እላለሁ፡፡