“ቤት” ማለት የሰው ልጅ መሰረታዊ ፍላጎቶች ከሚባሉት ከምግብና ከልብስ በኋላ የሚመጣው ነው፡፡ ወይም አነስ ባለ ቃል “መጠለያ”፡፡ ታዲያ የሰው ልጅ ሆኖ ተፈጥሮ እነዚህ ፍላጎቶች ሳይሟሉለት መኖር ምን ይባላል፡፡ በእርግጥ እንኳን እንደ ኢትዮጵያ ባለች ድሃ አገር በጣም በለፀገች በምትባለው፣ ሰማይን በአንድ አይናቸው የሚጠቅሱ ፎቆች ባሉባት አገር (ከፔንታጎን መንትያ ህንፃዎች ጀምሮ፤ አሁን በህይወት ባይኖሩም)፣ ከዓለም የበላይ ነኝ በምትለው፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፅ/ቤት የሚገኝባት፣ ልዕለ-ኃያል ነኝ በምትለው፣ ሥመ-ጥር ባለፀጋዎች ያሉባት አሜሪካን እንኳን ቤትና መጠለያ የሌላቸው ብዙዎች ናቸው፡፡ ግን በእኛ ሀገር ላይ በጣም ይብሳል፡፡ ቤት የሌለውን ከመቁጠር እኮ እውነቴን ነው የምላችሁ ያለውን መቁጠር ይቀላል፡፡ ምክንያቱስ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በግምት ከ60 በመቶ በላይ የሚሆነው ህዝብ የሚኖረው በኪራይ ነው እኔ እንደሚገባኝ፡፡ ለዛውም አከራዮች እንደ ሎሌ ሆነው እንደልባቸው እየፈነጩበት፡፡ ከቀሪዎቹ 40 በመቶዎች ደግሞ ቢያንስ 35 በመቶው እንደ ቤት በማይቆጠሩ የተቀዳደደ የድሃ ብርድ ልብስ የሚመስል ጣሪያ ባላቸው፤ ውሃ በነፃ የሚያስገቡ ማለቴ ነው፤ በእነዚህ ቤቶች ውስጥ ነው የሚኖሩት፡፡ ስለዚህ ደልቶት የሚኖረው ህዝብ ከ5 በመቶ በላይ ይሆናል ብዬ አላስብም፡፡ ታዲያ ይህ ሆኖ እያለ ቤት (ኮንዶሚኒየም) እየሰሩ መስጠት ለምን ዘግይቶ ተጀመረ? በእርግጥ የተፈናቀሉ ሰዎችን በእጅጉ እየጠቀመ ነው፡፡ ነገር ግን በ1997 ዓ.ም. ከተመዘገቡት ውስጥ እስካሁን የደረሳቸው ግማሽ እንኳን አልደረሱም፡፡ ለምንድን ነው መሰራቱ ካቀረ በብዛት ተሰርቶ በቤት እጦት ለሚሰቃዩ ነዋሪዎች የማይበረከተው፡፡ ዞሮ ዞሮ ገንዘብ ይከፍሉበታል፡፡ እናም እኔ የምለው የሚሰሩት ቤቶች ጥራታቸውን ጠብቀው፣ ዘመን የሚሻገሩ ሆነው ቢሰሩ ምንድን ነው ኃጢያቱ? ይቅርታ አድርጉልኝና እዚህ አገር የሚሰሩ ስራዎች ጠቅላላ ሲሰሩ ከ20 ዓመት በላይ ወደፊት የማይሻገሩ ስራዎች ናቸው የሚሰሩት፡፡ የወደፊቱ ትውልድ ታሳቢ ተደርጎ ቢሰራ እኮ ለጊዜው ነው ትንሽ ወጪ የሚጠይቀው እንጅ ለሀገሪቷ መፃኢ ህይወት በጣም ጠቃሚ ነው፡፡ በሌሎች ያደጉት ሀገራት እኮ በ18ኛው ክፍለ ዘመን የተሰሩ ህንፃዎች ናቸው ከመኖሪያነት ጀምሮ እስከ ቤተ-መንግስትነት የሚጠቀሙት፡፡ ለዚህም ነው ለግንባታ የሚወጣውን ወጪ ለሌሎች የልማት ስራዎች እያዋሉ ሊመነደጉ የቻሉት፡፡ አሁንም እኮ ከአሁን በፊት 3000 ዘመን እንዳደረግነው ልንቀጥል ነው፡፡
ስለሆነም እኔ የምለው የሚሰሩት ቤቶች ጥሩ አቅምና እድሜ እንዲኖራቸው ተደርገው ቢሰሩ ጥሩ ነው፤ የማንም አሸዋና ሲሚንቶ በትክክል ቀላቅሎ በማይሰራ ተለማማጅ ኢንጂነር ነኝ ባዮች መለማመጃ ሆኖ እንዳይቀር፡፡ ልክ በቅርቡ እንደተስተዋለው በጀሞ ኮንዶሚኒየም ሰዎች ውስጥ እያሉ እንዳዘመመው ቤት፡፡ በዚህ ከተቀጠለ መጨረሻው አያምርም፡፡
No comments:
Post a Comment