Monday, September 8, 2014

የጳጉሜ ወር ጣጣ

ጳጉሜ እንደምናውቀው የሀገራችን ኩራት የሆነች፣ “13 months of sunshine” እየተባልን በዓለም አቀፍ ደረጃ የምንኩራራባት፣ አምስትና ስድስት ቀናት እየሆነች የምታደናግረን፣ አንድ ወር ትሞላለች ብለን ድርቅ ብለን ራሳችን ላይ የለጠፍናት ሚጢጢ ወር ናት፡፡ በእርግጥ ከፈረንጆቹ የፀሃይ ዑደት አቆጣጠር እና ከአረቦቹ የጨረቃ ዑደት አቆጣጠር ዘዴዎች በእጅጉ የተለየ የአቆጣጠር ዘይቤ አለን፤ በኢትዮጵያ ውስጥ፡፡ በጣም የሚገርመው ደግሞ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ አራት ወቅቶችን በጠበቀ መልኩ ምንም ሳይዛነፉ እንዲታዩ የሚያደርግ የቀን አቆጣጠር ነው ያለን፡፡ ይህች ወር ግን ተቀጣሪዎች (የመንግስት) ምንም ሳያገኙ ወዛቸውን ሰጥተው ያለደመ-ወዝ በነፃ ህዝቡን የሚያገለግሉባት ወር ነች፡፡ ስለዚህ ይህች ወር ለሀገራችን በነፃ የሆነ ነገር የምናበረክትባት ድንቅ ወር ነች፡፡ በእርግጥ ወር አትባልም ሳምንት እንበል፡፡ ምክንያቱም ለክፍያ ሲሆን ሳምንት፤ ለዘመን አቆጣጠር ሲሆን ግን ወር ነቻ፡፡
ታዲያ በዚህች ጳጉሜ ወር የተነሳ ሰሞኑን ከቤት አከራዬ ጋር እንደጭቅጭቅ ነገር አጋጥሞኛል፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው፤ ብዙ ጊዜ ተከራይቼ ስኖር የጳጉሜ ወርን ያስከፈለኝ የለም፡፡ ይህችኛዋ ወይዘሮ ግን “የጳጉሜ ወር ኪራይ ትከፍላለህ” አሉኝ፡፡ እኔንስ ማን ችሎኝ፡፡ “እኔ የህዝብ አገልጋይ የመንግስት ሰራተኛ ነኝ፤ ይህችን ወር በነፃ እንደማገለግል አያውቁም ወይ” ስላቸው “እኔ ስለሱ የሚያገባኝ ነገር የለም፤ አኔ የማውቀው አንድ ወር 30 ቀን እንደሆነ ነው፤ ይህች 5 ቀን ደግሞ ተጨማሪ ነች፤ ስለዚህ ትከፍላለህ፤ ትከፍላለህ” አሉኝ፡፡ እኔም ማምረራቸውን ሳውቅ መለስ አልኩና “እኔ የማውቀው በዓመት ውስጥ 12 ወራት እንዳሉ ነው፡፡” አልኩ:: የተማርነውም እንደዚህ ነው፡፡ ግን ጳጉሜን እኮ ከአሁን በፊት እንደምኮራባት ለብዙ ሰዎች አውርቻለሁ፡፡ “ከዚህም በተጨማሪ ፈረንጆች ጋር 12 ወር ነው ያለው፡፡ አንድ ወር 31፣ 29፣ 30 ወይም 28 ቀናት ሊኖሩት ይችላሉ፡፡” ስላቸው “የኔ ልጅ እኔ ኢትዮጵያዊ ነኝ፤ የፈረንጅ አቆጣጠር እዚህ ምን አመጣው፡፡” ተባልኩ፡፡
አላዋጣኝ ሲል የተማፅኖ ዓይነት ትምህርት ልሰጣቸው ፈልጌ “የዜግነት ግዴታዎን በዓመት ውስጥ ለ5 ቀናት በነፃ ቢያኖሩ ምኑ ላይ ነው ነውሩ፡፡” ልላቸው አሰብኩና ተውኩት፡፡ ምክንያቱም የመብራት፣ የውሃ፣ የሽንት ቤት በነፃ የሚገኝ ይመስልሃል ብለው እንደሚመልሱልኝ አውቃለሁ፡፡ መቼም ይህች የአገልግሎት ክፍያ በወር ከ10 ብር ላትበልጥ ነገር የአዲስ አበባ አከራዮችን እንዴት እንደሚያንጨረጭራቸው አይገባኝም፡፡ እነሱ ለጋገሩበት ምጣድ ተከራዩን ማስከፈል ይፈልጋሉ፡፡
እና ምን ለማለት ፈልጌ ነው የሚመለከተው አካል ወይ እንደኔ ዓይነቱ ለጳጉሜ ወር ክፍያ እንዲያገኝ አለበለዚያም የቤት አከራዮች እኩል የዜግነት ግዴታቸውን እንዲወጡ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ ምክንያቱም ጳጉሜ የዓመቱ “ቫት” ነች፡፡ የሚከነክነኝን ነገር ማንሳት ስለፈለኩ ነው እንጂ ጳጉሜማ አንዷ የቱሪስት መስህብ እኮ ናት፡፡


Wednesday, March 19, 2014

ከ‹‹እንጃ›› በስተጀርባ

ሪፖርተር ጋዜጣ ላይ ደመቀ ከበደ የተሰኘ ገጣሚ ያቀረባት ግጥም ስለመሰጠችኝ ላካፍላችሁ ወደድኩ፡፡

==========

እኒያ የኔ ሰዎች

ከወንዝ ወዲያ ማዶ - በሩቅ የማያቸው

‹‹አትመጡም ወይ›› ብዬ - ለምጠይቃቸው

ከአፍ የሚወጣቸው

አንድ ነው ቃላቸው

‹‹እንጃ›› ነው መልሳቸው፤

እኒህም የኔዎች

አጠገቤ ያሉ - ሰርክ የማገኛቸው

ያልገባኝን ጉዳይ - ሁሌ ሳዋያቸው

ምንም ሳይዛነፍ - ‹‹እንጃ›› ነው መልሳቸው፤

‹‹ ከ‹እንጃ› ምሶሶና - ከ‹እንጃ› ባላ፣ ማገር

በ‹እንጃ› ባይ አናፂ - በታነፀች አገር

ከ‹እንጃ› ማለት በቀር

ለጥያቄ ሁሉ - ምላሽም አልነበር?››

ብየ እጠይቃለሁ

ብየ እጨነቃለሁ

ከጥያቄ ጋን ውስጥ - ጥያቄ እጠልቃለሁ፤

የምሬን እኮ ነው፤

‹‹ከ‹እንጃ› ባይ አገሬ

ከ‹እንጃ› የተሻለ - የአገር ምላሽ ባገኝ

‹ለምን?› አስረግዞ - ‹ለምን?› የወለደው - የሚያንገበግበኝ

ምላሽ ያጣሁለት - ጥያቄ ነበረኝ፤››

ብዬ እተክዛለሁ

ከጥያቄዬ ላይ - ጥያቄ እመዛለሁ፤

‹‹ማንን ነው ማዋየው - ወይ የማማክረው

የልቤ ጥያቄ - ልቤን ተረተረው፤››

እያልኩ አስባለሁ - ድንገት እነጉዳለሁ

ከጥያቄዬ ጋር - እወጣ እወርዳለሁ፤

ቢጨንቀኝ ጊዜ እንጂ፤

በ‹‹እንጃ›› አገር ተፈጥሮ - በ‹‹እንጃ›› ምላሽ አድጎ - ‹‹እንጃ›› ሲል ለኖረ

ከ‹‹እንጃ›› ማለት በቀር - ከ‹‹እንጃ›› የተሻለ - መልስም አልነበረ፤

ሀቅ ይኸውላችሁ፤

በዚች አገሬና - በዚች አገራችሁ

‹‹ምን ይበጀን ይሆን›› - ለሚል ጥያቄዬ - ለሚል ጥያቄያችሁ

‹‹እንጃ›› ነው ምላሹ - ‹‹እንጃልህ፣እንጃልሽ›› - ወይም ‹‹እንጃላችሁ››፡፡

© ደመቀ ከበደ

Monday, March 17, 2014

ቴሌ ከማገናኘት ወደ ማቆራረጥ

አማኑኤል ሆስፒታል ከሚባል የፌስቡክ ገፅ ላይ ከታች የተለጠፈውን ምስል ሳየው እኔንም የሚኮረኩረኝ ጉዳይ ስለሆነ ለእናንተም ለማካፈል ወደድኩ፡፡ መቼም ቴሌ ሰው ከሰው ለማቆራረጥ እንጂ ለማገናኘት እየሰራ አይደለም፡፡ እንዲያውም እንደኔ እንደኔ በቴክኖሎጂና መገናኛ ሚኒስቴር ስር ከሚሆን ማቆራረጥ የሚለውን ቃል ለመጠቀም ሲባል ተቋራጭ ድርጅቶች ውስጥ ቢገባ ይሻላል፡፡ ተቋራጭ የሚለው ቃል ኮንትራክተሮችን እንደሚመለከት ባውቅም ሌላ ቃል ላገኝ ስላልቻልኩ ነው፡፡ የቴሌ ኃላፊዎች ሁልጊዜ በተጠየቁ ቁጥር ከ6 ወር በኋላ ይስተካከላል፤ የምትል መልስ አለቻቸው፡፡ ነገር ግን እስካሁን ስንት 6 ወራቶች አለፉ፤ ስራውም አልተሰራም፤ እኛም ከወዳጅ ዘመዶቻችን ጋር መቆራረጣችን ቀጥሏል፤ እስኪ የሚቻል ከሆነ የቤት ስልክ ከነገመዱ ይዞ መዞር መሞከሩ ሳይሻል አይቀርም፡፡

1969212_595442210534076_435274582_n

Wednesday, February 12, 2014

ሶስት ጉልቻ

መቼም በዚህ ዘመን ተጋቢ በዝቷል፡፡ ያው ሰው ሲጋባ ከሁለት ወደ አንድ እንደሚቀየር ሁሉ ጋብቻን ፈቅደውና ወደው፤ አበድኩልሽ፣ ሞትኩልህ ብለው ጎጆ የሚቀልሱ በበዙበት አገር በአንፃሩ ደግሞ ጋብቻን የሚሸሹ ወንደ-ላጤዎችና ሴተ-ላጤዎች ደግሞ ቤት ይቁጠራቸው እንጂ ቆጥሮ ማን ሊዘልቃቸው፡፡ የሚገርመው አንዳንዶቹ ጋብቻን ከመፍራታቸው የተነሳ እስከ 50 ዓመት እንዲያውም ተገንዘው እስከሚወጡ ድረስ እናትና አባታቸው ቤት ማሙሽና ሚሚ ተብለው የሚኖሩ ብዙ አሉ፡፡ ከዚህ በተጓዳኝ ተጋብተው፣ ወልደው ከብደው፣ የወርቅ ኢዮቤልዮ የሚያከብሩ በድሮ ዘመን የተባረከ ትዳር የሰጣቸው በጣት የሚቆጠሩ አባትና እናቶች እንዳሉት ሁሉ፤ በዚህ ዘመን ስንመለከት ግን ተጋብተው በማግስቱ ሁላ የፍርድ ቤት ደጃፍ የማይረግጥ ተጋቢ የለም፡፡ ለዚህም ይመስለኛል አንዳንዶቹ ከማግባት ይልቅ አርፈው የእናትና አባታቸው ቤት የሚቀመጡት፡፡ ከሚጋቡት ጥንዶች የበለጠ በየጊዜው የሚፋቱ ጥንዶች በዝተዋል፡፡ በእርግጥ የሚፋቀሩና የሚተሳሰቡ ወጣት ጥንዶች የሉም ማለቴ አይደለም፡፡ ያው በላጤነት የተለመደ ነፃነት እና ትዳር ውስጥ ሊያጋጥሙ የሚችሉትን ነገሮች ቀድሞ አስቦና ተዘጋጅቶ አለመግባት እንዲሁም ከተጋቡ በኋላ የፍቅር መቀነስ ዋና ዋናዎቹ ምክንያቶች እንደሆኑ ይነገራሉ፡፡ ለማንኛውም “ትዳር ጣፋጭ ነው” እንዳለው ደራሲ በእውቀቱ ጣፋጭ ለማድረግ እንጣር፡፡1509313_799126630117386_1591916346_n

Ethiopian Overlooked and Underutilized Sector - Agriculture

Agriculture is the prominent sector of Ethiopia which millions of lives depend on for centuries. The share still stands high compared ...