Friday, November 29, 2013

ስለ ኤግዚቢሽን…

ሚሊኒዬም አዳራሽ የተካሄደ የኮንስትራክሽን እና ፈርኒቸር ኤግዚቢሽን ነበር፡፡ እና ቅዳሜ ዕለት ጓደኛዬ ጋር ወደዛው እናመራለን፡፡ አንድም በትክክል ስለራሱ ድርጅት እና ምርት የሚያስተዋውቅ ሰው ይጠፋል? በየካውንተሩ ሄድን ግን አንዱ ሲፈልገው ዝም ብሎ ይገለፍጣል፤ የሱን ጥርስ ማዬት የናፈቀን ይመስል፡፡ ሌላው ለንቦጩን ጥሎ ፀጥ ብሎ በራሱ የሃሳብ ማዕበል ውስጥ ይጓዛል፡፡ ታዲያ በዚህ ሁኔታ ኤግዚቢሽን ለሀገሪቷ ለምን ጠቀማት? እኔ መቼም እስከማውቀው ኤግዚቢሽን ላይ እንዲሳተፉ የሚፈቀድላቸው ኩባንያዎች የተሻለ አገልግሎት ወይም ምርት ያላቸውና የገበያ ዕድል እንዲያገኙ የሚያስችል፣ ቀጥታ ከተገልጋዮች ጋር የሚገናኙበት እና ስለ ኩባንያቸውም የሚያስተዋውቁበት ነው፡፡ ይህ ሆኖ እያለ ግን የሚታየው ነገር የተገላበጠ ነው፡፡

ፉገራ

እኛ ሰፈር ፍቅረኛሞች አሉ እና ሴቷ በጣም ረዥም ሆና በተቃራኒው ደግሞ ወንዱ አጭር ነው፡፡ መቼም ፍቅር እንኳን ቁመት ሌላም ነገር የማይወስነው ጠንካራ ኃይል ያለው ቁርኝት እንደሆነ አውቃለሁ፡፡ እናም ለምን ተፋቀሩ ብዬ የሞኝ አፌን አልከፍትም፡፡ ግን እንዲሁ ለመቀለድ ያህል የሰፈር ልጆች ምን ቢሉ ጥሩ ነው? “በቁመት ስለማይደራረሱ አብረው ቁመው እንኳን በስልክ ነው የሚነጋገሩት” ብለው ቁጭ፡፡ የኛ ሰው መቼም አቃቂር ለማውጣት የሚችለው የለም፡፡ እነሱ ተመቻችተው ነው እየኖሩ ያሉት፡፡ እኔ ግን ስላሳቀኝ ለናንተም ልንገራችሁ ብዬ ነው የፃፍኩት፡፡

Tuesday, October 29, 2013

ስለ ዳና ድራማ ክፍል 24

ዳና ተከታታይ የቴሌቪዝን ድራማ መተላለፍ ከጀመረ እነሆ 2ኛ ምዕራፍ፤ 24ኛ ክፍል ላይ ደርሷል፡፡ እና በዚህ ክፍል “አይዳ” የተባለችው ገፀ-ባህሪ “እቴቴ” ከተባለችው ጋር በሚያደርጉት የስልክ ቃለ-ምልልስ ላይ “አይዳ” የተቀመጠችበት ፊት ለፊት የሚገኘው ጠረጴዛ ላይ አስተውላችሁ ከሆነ የተዘቀዘቀ የኢትዮጵያ ባንዲራ ወይም ሲዘቀዘቅ የሴኔጋል የሆነ ባንዲራ ይታያል፡፡ ይህ በቀላሉ ታይቶ ችላ የሚባል ነገር አይደለም፡፡ እኔ ትንሽ ስህተት አይቼ ለማጣጣል ሳይሆን፤ ቁጥር ከአንድ ይጀምራል፣ ስህተትም እንዲሁ ከትንሽ ነው የሚጀምረው ብዬ ስለማምን ነው፡፡ ይህ ፕሮግራም በዓለም ዙሪያ የሚተላለፍ እንደመሆኑ መጠን ኢትዮጵያውያን ያልሆኑ ሰዎች የኢትዮጵያ ባንዲራ እንደዛ ሊመስላቸው ይችላል፡፡ ለማንኛውም ከዳይሬክተሩ ጀምሮ እስከ ተራው አርቲስት ድረስ እንደዚህ ዓይነት ነገሮችን በትክክል አስተውለው መስራት አለባቸው ባይ ነኝ፡፡ ይህ የሚመጣው ቸልተኛ ከመሆንና ለስራው ትኩረት ካለመስጠት ይመስለኛል፡፡ ምንም እንኳን በዘርፉ ባለሙያ ባልሆንም ካሜራ የሚይዘውን ቦታ ሁሉ በጥንቃቄ ማስተዋል ያስፈልጋል፡፡ ለዚህም ነው እኮ ኢዲቲንግ ያስፈለገው፡፡ በእርግጥ ተከታታይ ድራማ መስራት አሰልቺ እንደሆነ እሰማለሁ፡፡ ነገር ግን ስራዬ ተብሎ ከተያዘ የሚያቅት ነገር የለም፡፡ ይህን በአጋጣሚ አነሳሁት እንጂ በሚወጡት ፊልሞች ሁሉ አቃቂር ማውጣት ቀላል ነው፡፡ ከካሜራ ጥራት ጀምሮ እስከ ድምፅ ጥራት እንደዚሁም በታሪክ ፍሰታቸው እዚህ ግቡ የማይባሉ ፊልሞች ይወጣሉ እኮ፡፡ ይህን ከማድረግ አራት፣ አምስት ዓመት ፈጅቶ በጥንቃቄ ጥራት ያለውና ሃገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚያስጨበጭብና ለኦስካር የሚታጭ ፊልም መስራት አይሻልም ወይ?

Tuesday, October 22, 2013

የመዲናችን ህንፃዎች የወል ባህሪ

“አዲስ አበባ፣

ዳርዳሯ አበባ፣

ውስጧ ሌባ፡፡”

የተባለላት አዲስ አበባ፤ ዋና ከተማ የሆነችበትን ጊዜ ለመቁጠር ወደኋላ አፄ ሚኒልክ የነገሱበትን ጊዜ ማስላት ያስፈልጋል፡፡ የዛን ጊዜ እቴጌ ጣይቱ እንጦጦ ላይ ሆነው ቁልቁል ሲመለከቱ ደስ አለቻቸውና “አዲስ አበባ” ብለው ሰይመው መኖሪያቸውን ወደዚህች ከተማ አዛወሩ፡፡ እነሆ ከዛን ጊዜ ጀምሮ አዲስ አበባ ቀስ በቀስ በእድገት ጎዳና ላይ ትገኛለች፡፡ ፎቅ መሰራት የተጀመረው በቅርብ ጊዜ ቢሆንም፡፡ ያን ሁሉ አልፋ አሁን ከተማዋ የፎቆች ውድድር የሚካሄድባት ይመስላል፡፡ ከወር በኋላ ቆይተህ የሆነ ሰፈር ብትሄድ አዳዲስ ፎቆች በቅለው ነው የምታገኘው፤ መንገድ የተሳሳትክ እስከሚመስልህ ድረስ ማለት ነው፡፡ እና አብዛኛዎቹን ፎቆች የሚያመሳስላቸው አንድ እውነታ አለ፤ ይኸውም የመስታውት ብዛት ነው፡፡ ፎቅ ያለመስታውት የማይሰራ ይመስል፡፡ ባለቤቶቹም የሚፈልጉት፣ አርክቴክቸሮቹም ዲዛይን የሚያደርጉት ተመሳሳይ ነገር፤ መስታውት በመስታውት የሆነ ቤት ነው፡፡ እኔምለው መስታውት እርካሽ ነው እንዴ? ከብሎኬት ጋር ሲነፃፀር፡፡ ለማንኛውም ይህን ስሌት ለመሃንዲሶች እንተወውና እንለፍ፡፡ ይህ የመስታውት ብዛት ከተማዋን ምድረ-በዳ እያደረጋት ነው፡፡ ምን ለማለት ፈልጌ ነው የመስታውቱ ነፀብራቅ ፊት ላይ ሲያርፍ ያቃጥላል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ እርግጠኛ ነኝ እስካሁን የዓይን ብሌኑ የተቃጠለ ሰው ይኖራል፡፡ ቤት ይቁጠረው ብለን እንተወው እንጂ፡፡ የመስታውት በረሃ ዋጠን እኮ ምን ይሻላል ትላላችሁ? ለዚህ ማስተማሪያ የሚሆን ማንኛውንም ፎቅ የሚያስንቅ ያየሁት ፒያሳ ላይ ያለው “እናት ህንፃ” ብቻ ነው፡፡ ሌሎቹ ሁሉም አንድ መሃንዲስ ዲዛይናቸውን የሰራቸው ይመስል ተመሳሳይ ናቸው፡፡ እኔምለው ዲዛይን ያለመስታውት አይቻልም አያምርም ያለው ማነው? ለማንኛውም መንግስትም የድርሻውን ቢወጣና ዓይናችን ከመጥፋቱ በፊት መፍትሄ ቢያፈላልግ፤ ባለሙያዎቹም ሙያቸውን የሚያሳድግ ነገር ቢሰሩ መልካም ነው እላለሁ፡፡

Friday, October 18, 2013

የጨዋታ መልስ ድባብ

የኢትዮጵያ እና የናይጄሪያ ብሔራዊ ቡድን ጨዋታ ዕለት ማታ የአልኮል ገበያ ደርቶ ነበር፡፡ ለምን መሰላችሁ፤ መቼም የኛን ሀገር ነገር ከኔ የበለጠ ታውቁታላችሁ፤ ስናሸንፍ ለደስታ ተብሎ መጠጥ ቤት፤ ግብዣ በግብዣ፡፡ ስንሸነፍም እንደዚሁ ለንዴት ማስወገጃ ተብሎ መጠጥ ቤት፡፡ እና የአሁኑ ደግሞ ኢትዮጵያ ትሸነፋለች ብለው ቁማር ያስያዙ አገር ወዳድ ያልሆኑ የናይጄሪያ ደጋፊዎች በደስታ ጮቤ ረግጠው መጠጥ ቤት ያሳልፋሉ፡፡ በአንፃሩ ደግሞ ኢትዮጵያ በመሸነፏ ቅስማቸው የተሰበረ ንፁህ የኢትዮጵያ ደጋፊዎች እና ኢትዮጵያ ታሸንፋለች ብለው የቆመሩትም ጭምር ንዴቱን ለመርሳት ብለው መጠጥ ቤት ከትመው ነው ያመሹት፡፡ እና በዚህ መሃል የሃገሪቷ የመጠጥ ፍጆታ ከፍ ሳይል አይቀርም ብዬ እጠረጥራለሁ፡፡ የሃገሪቷ GDP በዚህን ያህል ምጣኔ ባያድግም በዕለቱ፡፡ በመሸነፋችን ላዘናችሁ ኢትዮጵያውያን በመልሱ ጨዋታ እናሸንፋለን አይዟችሁ እላለሁ፡፡ ኢትዮጵያ ትሸነፋለች ብላችሁ ቁማር የበላችሁ ሟርተኞችም ልብ ይስጣችሁ፤ ተመሳሳይ ይሆናል ብላችሁ እንዳትሸወዱ፡፡

Thursday, October 17, 2013

የስም መመሳሰል ወይስ የስም መገለባበጥ

ሰሞኑን አንድ የገጠመኝን ልንገራችሁ፡፡ ሜክሲኮ አካባቢ ነው፡፡ አንድ ከክፍለ ሀገር የመጣ ልጅ ከአውቶብስ ተራ ተነስቶ ታክሲ ይዞ ሜክሲኮ ደርሷል፡፡ እና ወደ ለገሃር እያመራ እያለ እኔጋ ተገናኘንና “የሞጆ መንገድ ወዴት ነው” ብሎ ጠየቀኝ፡፡ እኔም ሞጆ ከአዲስ አበባ ውጪ እንደሆነና ሚኒ ባስ ይዞ ወደ ደብረዘይት መሄድ እንደሚችል ስነግረው፡፡ “ሞጆ ኮንዶሚኒየም ያለበት” ሲለኝ ነቄ ብዬ “ጀሞ ኮንዶሚኒየም ማለትህ ነው” አልኩት፡፡ በዚህ ጊዜ ልጁ “አዎን” አለ፡፡ ከዛ ታክሲ መያዣውን አሳየሁትና እብስ አልኩኝ፡፡ አስቡት እስኪ ከአውቶብስ ተራ ለገሃር ድረስ የመጣው የሞጆ ታክሲ ሊይዝ ነበር፡፡ እዛ ደርሶ ያው መመለሱ አይቀርም ነበር፡፡ አሁን ይኼ “የስም መመሳሰል” ነው ወይስ “የስም መገለባበጥ”፡፡

Ethiopian Overlooked and Underutilized Sector - Agriculture

Agriculture is the prominent sector of Ethiopia which millions of lives depend on for centuries. The share still stands high compared ...