Thursday, May 23, 2013

የመብራት ያለህ…

አሁን አሁን የመብራትና የስራ እንዲሁም የመብራትና የሰው ቁርኝት በጣም የሚገርም ነው፡፡ ያለመብራት መስራት ድሮ ቀረ እኮ፡፡ ምክንያቱም ሁሉ ነገር በኮምፒዩተር ነው የሚሰራው፡፡ በተለይማ በመስሪያ ቤቶች አካባቢ የሚስተዋለው መብራት ሲጠፋ የሆነ ብርሃን ያለበት አካባቢ የቢሮው ሰራተኛ ይሰበሰብና መዓት ወሬ ይቸረችራል፡፡ በቤት ጉዳይ፣ በመብራት ጉዳይ፣ ስለሀገሪቷ ተጨባጭ ሁኔታ፣ ስለ ምሳ፣ ወ.ዘ.ተ… ብቻ ምን አለፋችሁ World Atlas ውስጥ የሌለ ነገር ሁሉ ይሰማል፡፡ እናም ምን ልላችሁ ነው፤ የሰው ልጅ ከህያውነቱ ወደ ሮቦትነት ተቀይሯል፤ መብራት ሲጠፋ ልክ እንደ ሮቦት ቀጥ፡፡ ምንም ያክል በእጅ የሚሰራ ስራ ቢኖር እንኳን መብራት ከጠፋ የስራ ሙድ አብሮ ይጠፋል፡፡

This shows the ultimate dependency syndrome of electricity (power). In this world we live in right now, nothing can be done without power and computer. Because it is the time of Artificial Intelligence than natural intelligence.

መብራት ኃይል ደግሞ የሆነ የቁማር ጨዋታ ይጫወት ይመስል ይህን ሁሉ ነገር እያወቀ ጢባ ጢቤ ይጫወታል፡፡ የሚገርመው እኮ የመብራት ኃይል መስሪያ ቤት ራሱ መብራት ከጠፋ ስራ ማቆሙ ነው፡፡ ይህ ሁሉ ተጠራቅሞ የሀገሪቷን ኢኮኖሚ እንደሚያሽመደምደው ሳይታለም የተፈታ፤ ፀሃይ የሞቀው እውነታ ነው፡፡ ባለጉዳይ ይጉላላል፤ ፋብሪካዎች ይቆማሉ፤ የተጀመረ ስራ እንደተጀመረበት ሰዓት ምርታማ ሆነህ መብራት ከመጣ በኋላ መቀጠል አትችልም፡፡

ስለሆነም በእነ ጊቤ፣ ተከዜ፣ አዋሽ፣ እና አባይ አምላክ መብራት ኃይል ወደፊቱን ቢያስተካክል ጥሩ ነው፡፡ “አንድ ጎልና አንድ ባል አያስማምንም” እንደሚባለው መብራት ኃይል እና ቴሌ አንድ ለሀገሪቷ ስለሆኑ አማራጭ መጠቀም አልተቻለም፡፡ ስለዚህም ነው እንደፈለጉ የሚጫወቱብን፡፡ ለማንኛውም ይህ ከላይ የጠቀስኩት ሁሉ እሮሮ መስተካከል አለበት ለማለት ያህል ነው፡፡

Tuesday, May 21, 2013

አይ ቤት….

“ቤት” ማለት የሰው ልጅ መሰረታዊ ፍላጎቶች ከሚባሉት ከምግብና ከልብስ በኋላ የሚመጣው ነው፡፡ ወይም አነስ ባለ ቃል “መጠለያ”፡፡ ታዲያ የሰው ልጅ ሆኖ ተፈጥሮ እነዚህ ፍላጎቶች ሳይሟሉለት መኖር ምን ይባላል፡፡ በእርግጥ እንኳን እንደ ኢትዮጵያ ባለች ድሃ አገር በጣም በለፀገች በምትባለው፣ ሰማይን በአንድ አይናቸው የሚጠቅሱ ፎቆች ባሉባት አገር (ከፔንታጎን መንትያ ህንፃዎች ጀምሮ፤ አሁን በህይወት ባይኖሩም)፣ ከዓለም የበላይ ነኝ በምትለው፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፅ/ቤት የሚገኝባት፣ ልዕለ-ኃያል ነኝ በምትለው፣ ሥመ-ጥር ባለፀጋዎች ያሉባት አሜሪካን እንኳን ቤትና መጠለያ የሌላቸው ብዙዎች ናቸው፡፡ ግን በእኛ ሀገር ላይ በጣም ይብሳል፡፡ ቤት የሌለውን ከመቁጠር እኮ እውነቴን ነው የምላችሁ ያለውን መቁጠር ይቀላል፡፡ ምክንያቱስ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በግምት ከ60 በመቶ በላይ የሚሆነው ህዝብ የሚኖረው በኪራይ ነው እኔ እንደሚገባኝ፡፡ ለዛውም አከራዮች እንደ ሎሌ ሆነው እንደልባቸው እየፈነጩበት፡፡ ከቀሪዎቹ 40 በመቶዎች ደግሞ ቢያንስ 35 በመቶው እንደ ቤት በማይቆጠሩ የተቀዳደደ የድሃ ብርድ ልብስ የሚመስል ጣሪያ ባላቸው፤ ውሃ በነፃ የሚያስገቡ ማለቴ ነው፤ በእነዚህ ቤቶች ውስጥ ነው የሚኖሩት፡፡ ስለዚህ ደልቶት የሚኖረው ህዝብ ከ5 በመቶ በላይ ይሆናል ብዬ አላስብም፡፡ ታዲያ ይህ ሆኖ እያለ ቤት (ኮንዶሚኒየም) እየሰሩ መስጠት ለምን ዘግይቶ ተጀመረ? በእርግጥ የተፈናቀሉ ሰዎችን በእጅጉ እየጠቀመ ነው፡፡ ነገር ግን በ1997 ዓ.ም. ከተመዘገቡት ውስጥ እስካሁን የደረሳቸው ግማሽ እንኳን አልደረሱም፡፡ ለምንድን ነው መሰራቱ ካቀረ በብዛት ተሰርቶ በቤት እጦት ለሚሰቃዩ ነዋሪዎች የማይበረከተው፡፡ ዞሮ ዞሮ ገንዘብ ይከፍሉበታል፡፡ እናም እኔ የምለው የሚሰሩት ቤቶች ጥራታቸውን ጠብቀው፣ ዘመን የሚሻገሩ ሆነው ቢሰሩ ምንድን ነው ኃጢያቱ? ይቅርታ አድርጉልኝና እዚህ አገር የሚሰሩ ስራዎች ጠቅላላ ሲሰሩ ከ20 ዓመት በላይ ወደፊት የማይሻገሩ ስራዎች ናቸው የሚሰሩት፡፡ የወደፊቱ ትውልድ ታሳቢ ተደርጎ ቢሰራ እኮ ለጊዜው ነው ትንሽ ወጪ የሚጠይቀው እንጅ ለሀገሪቷ መፃኢ ህይወት በጣም ጠቃሚ ነው፡፡ በሌሎች ያደጉት ሀገራት እኮ በ18ኛው ክፍለ ዘመን የተሰሩ ህንፃዎች ናቸው ከመኖሪያነት ጀምሮ እስከ ቤተ-መንግስትነት የሚጠቀሙት፡፡ ለዚህም ነው ለግንባታ የሚወጣውን ወጪ ለሌሎች የልማት ስራዎች እያዋሉ ሊመነደጉ የቻሉት፡፡ አሁንም እኮ ከአሁን በፊት 3000 ዘመን እንዳደረግነው ልንቀጥል ነው፡፡

ስለሆነም እኔ የምለው የሚሰሩት ቤቶች ጥሩ አቅምና እድሜ እንዲኖራቸው ተደርገው ቢሰሩ ጥሩ ነው፤ የማንም አሸዋና ሲሚንቶ በትክክል ቀላቅሎ በማይሰራ ተለማማጅ ኢንጂነር ነኝ ባዮች መለማመጃ ሆኖ እንዳይቀር፡፡ ልክ በቅርቡ እንደተስተዋለው በጀሞ ኮንዶሚኒየም ሰዎች ውስጥ እያሉ እንዳዘመመው ቤት፡፡ በዚህ ከተቀጠለ መጨረሻው አያምርም፡፡

Thursday, May 16, 2013

የከፍተኛ መንግስት ባለስልጣናት የሀብት ምዝገባ

የኢትዮጵያ ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ከሁለት ዓመት በፊት ገደማ ጀምሮ እንደ አጀንዳ ይዞ በተለያዩ ሚዲያዎች ሲወራ ሰምተናል፣ አይተናል፣ አንብበናል፡፡ ኮሚሽኑ በተደጋጋሚ ቆጠራና ምዝገባ ከተጠናቀቀ በኋላ ለህዝብ ይፋ እንደሚሆን ቃል ገብቶ ነበር፡፡ ይሁንና ይኸው ከሁለት ዓመት በላይ በኋላም ምንም ጠብ ያለ ነገር የለም፡፡ የተሰማ ነገር የለም፡፡ 2005ም ሊያልቅ ነው፤ መስከረም ሊጠባ ነው፡፡ ሲጀመር እኛ ተቆጥሮ ይነገረን አላልንም፤ ከተባለ በኋላ ግን አፋችንን ከፍተን ስንጠብቅ ነበር፡፡ ነው ወይስ ተቆጥሮ አላልቅ አለ፤ የተበታተነ ንብረት ካለ ምናልባት፡፡ ባለስልጣኖቻችን እንደሆኑ እንግዲህ በPay roll ነው የሚከፈላቸው፡፡ እንበልና አንድ ባለስልጣን ከ83 ዓ.ም ጀምሮ ስልጣን ላይ ቢሆንና እስከ 2005 ዓ.ም በየወሩ 4,000 የኢትዮጵያ ብር የተጣራ ደሞዝ ቢከፈለው ሂሳቡ፡-

4,000ብር X 22ዓመት X 12ወራት = 1,056,000 ብር ይሆናል፡፡

ይህን የሚያጠራቅመው ደሞዙን ለምንም ነገር ባያውለው ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም ባለስልጣኖቻችን መቼም ማክያቶ ለመጠጣት ጊዜ የላቸውማ፡፡ ለነገሩማ እንደሚወራው ከሆነ እኮ የሚከፈላቸው ደሞዝ አነስተኛ ቢሆንም፤ ብዙ ጠያቂ አላቸው ነው የሚባለው፤ ልክ ሰሞኑን እንደተስተዋለው የጉምሩክ ባለስልጣና ኃላፊዎች በተግባር እንዳሳዩት ማለት ነው፡፡ ልክ በጃንሆይ ጊዜ ሲደረግ እንደነበረው ማለት ነው፡፡ አንድ ጉዳይ ለማስፈፀም በግ እየጎተቱ የሚሄዱበት ጊዜ ነበር፤ አሁን አድጎ በውጭ ምንዛሬ፣ በህንፃዎች፣ በፋብሪካዎች፣ ወ.ዘ.ተ… ሆኗል፤ ምክንያቱስ ከአገራችን እድገት አንፃር ነዋ፡፡ በነገራችን ላይ ሙስና ባይኖር እኮ አዲስ አበባችን እነዚህን በመሳሰሉ ረዣዥም ህንፃዎች አትሽቆጠቆጥም ነበር፤ ጠቀሜታውን ከዚህ አንፃር እንቃኘው፡፡

ወደ ዋናው ጉዳይ ልመልሳችሁና ይህች ተቆጥራ የምታልቅ የPay roll ገንዘብ እንዴት የህን ያህል ጊዜ እንደፈጀች ሊገባኝ አልቻለም፡፡ ቢሆንም በቀጣዩ ምርጫም ጊዜ ቢሆን እኛ እንዲነገረን እንፈልጋለን፡፡ በደሞዙ እየተሸማቀቀ፣ የቤት ኪራይ ከደሞዝ በላይ የሚከፍል፣ የሚበላው፣ የሚጎርሰው፣ የሚለብሰው፣ የሚጠጣው ያጣ የመንግስት ሰራተኛ (Civil Servant) ተብሎ ግብዳ ስም ወጥቶለት የሚኖር ስንቱ ነው መሰላችሁ፤ ብቻ “ቤት ይቁጠረው” ወይም “ሆድ ይፍጀው” ብለን እንለፈው እንጂ፡፡ “ሁሉን ሲናገሩት ሆድ ባዶ ይቀራል” ነው ያለችው ዘፋኟ፡፡ “Civil Servant” የሚለው ቃል “የህዝብ አገልጋይ” የሚል አቻ ትርጓሜ ያለው ሲሆን፤ የሚሰጠው ደሞዝና ክብር ግን በድሮ ጊዜ “ባሪያ” ተብለው እየተገረፉ ሲሰሩ ከነበሩት በጣም የወረደ ነው፤ ለዛውም የዛን ጊዜ ባሪያዎች የሚበሉት እስከሚጠግቡ ነው፤ ለሚኖሩበት ቤት አይጨነቁም፡፡ እና ምን ለማለት ፈልጌ ነው የህዝብ አገልጋዩ ተሰቃይቶ እንዲኖር የተፈረደበት ይመስል፤ እንዲሁ ቀን ያልፋል እያለ እየተንፏቀቀ እየኖረ ይገኛል፡፡ ይህ ሁሉ እሮሮ የሁሉም የመንግስት ሰራተኛ ነው፡፡ ኑሮ ሲወደድ፣ የእቃ ዋጋ ሲንር፣ የሚጠቀመው ነጋዴውና የግል ተቀጣሪው ነው፡፡ እነሰሱ አያግኙ ማለቴ አይደለም፡፡ ነጋዴዎች የገበያ ላይ ዋጋ ሲጨምሩ ለመንግስት ሰራተኛው ትንሽ ድጎማ ቢጤ ታስፈልጋለች ማለቴ ነው፡፡ ዋናውን ርዕሴን ትቼ ወደ እሮሮ ገባሁ እኮ፤ ይቅርታ ይህ ነገር ስለሚከነክነኝ ነው፡፡ ብዙ ጓደኞቼ የመንግስት ሰራተኛ በመሆናቸው የማየውን ነው ያወራሁት፡፡ ስለሆነም በመጨረሻ የባለስልጣኖቻችን ሀብት ተቆጥሮ፣ ሰባራ ሳንቲም ሳይቀር፣ እንዲነገረን እንፈልጋለን፡፡

Tuesday, April 23, 2013

ነጭ ወረቀትና ጥቁር ነጥብ


በጣም የሚዋደዱ ባልና ሚስቶች ነበሩ፡፡ እናም ፍቅራቸውን ለተመለከተ ሰው በጣም ያስቀናሉ፡፡ ይህን ሁሉ ዘመን በሰላምና በፍቅር ሲኖሩ ባልየው ለሚስቱ ታማኝ፣ ቤቱን አጠንክሮ የያዘና በፀባዩ የተመሰገነ ነበር፡፡ ታዲያ ከዕለታት አንድ ቀን ባልዬው ትንሽ ጥፋት ያጠፋና ሚስት ሆዬ ቡራ ከረዩ ትላለች፡፡ የዚህን ጊዜ ባል ምን ሆነሽ ነው፤ እስከዛሬ ያደረኩትን መልካም ነገር ዘንግተሽ እንዴት ዛሬ ይህችን ያልረባች ጥፋት አጋነንሻትብሎ ጠየቀ፡፡ የዚህን ጊዜ ሚስት ምን መሰለህ፤ እስኪ በምሳሌ ልንገርህ፤ አንድ ነጭ ወረቀት ላይ ትንሽ ጥቁር ነጥብ ብትኖር የበለጠ የሚታየው የቱ ይመስልሃልብላ ጥያቄውን በጥያቄ መለሰችለት፡፡ ባልም ጥቁር ነጥቡአለ፡፡ እሷም ይኸውልህ አለችው፤ ከወረቀቱ ይልቅ ትንሿ ነጥብ ጎልታ እንደታዬችህ ሁሉ ከብዙ ጥሩ ስራህ ይልቅ ይህች ትንሿ መጥፎ ስራ ጎልታ ትታያለችአለችው ይባላል፡፡
እናም የወንጀልና የቁርስ ትንሽ የለውም” ብለን እንደምድም፡፡

የስብሰባ አባዜ



ለሁለት ተሰብሳቢዎች ማይክሮፎን መጠቀም ምን የሚሉት ስልጣኔ፤ ምን የሚሉት ቅብጠት ነው ወዳጆቼ፡፡ አንደኛ ለጆሮ ጥሩ አይደለም፡፡ ሁለተኛም የመብራት ፍጆታ ይወስዳል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በስብሰባ ብዛት የተነሳ አንድ ሁለት ተሰብሳቢዎች ብቻ ቢሆኑም ትልቅ አዳራሽ ውስጥ ገብቶ ሰብሳቢው ድምፁን በማይክሮፎን ደብልቆ ሰበሰበ ለመባል ብቻ የሚደረግ ስር የሌለው ተግባር ነው፡፡ እኔማ አንዳንዴ ሳስበው የኢትዮጵያ ቀሪ ሀብትና ባህል ስብሰባ ብቻ ሆነ እንዴ እላለሁ፡፡ እውነቴን እኮ ነው የምላችሁ ለጥቃቅን ነገር ሁሉ ስብሰባ፤ ስራ ተዘግቶ፤ ደንበኛ እየተጉላላ፡፡ በተለይ በተለይ በመንግስት መስሪያ ቤቶች ላይ የሚስተዋለው ይኼው ነው፡፡ ደግሞ እኮ ከጥንት ጀምሮ ነው፤ በንጉሱ ጊዜም እንደዚሁ ወሬ ሲያሞቁ ይውሉና የህዝቡን ችግር ይዘነጉት ነበር፤ በደርግ ጊዜም ጓድ ሊቀመንበር በጦር ሜዳም ቢሆን ተናጋሪ በመሆናቸው ብዙ ያወራሉ፤ ይሰበሰባሉ፤ ያሁኑ ይባስ ደግሞ ሁልጊዜ ስብሰባ፡፡ እድገታችን በስብሰባ ብዛት የሚለካ ከሆነ አላውቅም ብቻ፡፡ እኔ እንደሚገባኝ በጋራ ውሳኔ የሚሻ ጠቃሚ ነገር ሲፈጠር ብቻ ነው ስብሰባ የሚያስፈልገው፡፡ 

ስለዚህ መቼም ስብሰባ ይጥፋ ብዬ አልሞግትም፤ ይልቁንም በወግና ባግባብ መሆን አለበት ብዬ ነው የምደመድመው፡፡

Thursday, April 18, 2013

አንበሳ አውቶባስ


የአዲስ አበባ እድሜ ጠገብ አንበሳ አውቶቡስ ድርጅት በቢሾፍቱ ባስ ከተሰራ ወዲህ የማስታወቂያዎች የደራ ገበያ ማሟሟቂያ ሆኗል፡፡ ክፍያ ይኑረው አይኑረው ባላውቅም ብቻ ድሮ የምናውቀው ቀይ በቢጫ ቀለም አንበሳ አውቶቡስ ዛሬ የኢንዶሚ፣ የአንቦ ውሃ እና ሌሎች ማስታወቂያዎች ጠቅላላ አካሉን ሸፍነውት ስንት ቁጥር እንደሆነ ራሱ ለማወቅ ያዳግታል፡፡ እኔማ ሳስበው እኛ ሀገር ውስጥ ስታንዳርድ እና ብራንድ ስም የሚባል ነገር ለምን አይኖርም እላለሁ፡፡ ላልረባ ጥቅም ከድሮ ጀምሮ ስንጠቀምበት ለምደነው የኖርንበትን ልማድ ቀይረው የማስታወቂያ ድርጅት አስመሰሉት እኮ፡፡

ስለሆነም፤ መንግስት ለሀገሪቷ መልካም ስም በማሰብ የማስታወቂያውን መጠን ራሱ በትንሽ ካሬ ሜትር ለክቶ ቢያደርግ ለራሱም ስታንዳርዱን ጠብቆ ለመቆየት እና ተሳፋሪም ከመደናገር ይድናል፡፡

Monday, April 15, 2013

የድሮና የዘንድሮ ልጅ ባጭሩ


አንድ ጓደኛዬ ያጫወተኝን ልንገራችሁ፡፡ ልጅ እያለን እንደ ስጥ ከቤት ውጪ ተጥለን እናታችን ገበያ ስትሄድ ለጎረቤት አደራ ሰጥታ፤ ምን ብላ?  “እትዬ ጎርፌ ዝናብ ከመጣ የተሰጣውን በርበሬ ስታስገቢ ልጁንም አብረሽ አስገቢው” ተብለን ነው ያደግነው፡፡ ምክንያቱስ ልጅ በሽ ነዋ፤ የዛን ጊዜ፡፡ አሁን ግን የተገላቢጦሽ ሆኗል፡፡ ልጅ ነው እናቱን ለሰው አደራ ሰጥቶ እንደልቡ የሚዞረው፤ ይህም ትዝ ካለችው ነው፡፡

Ethiopian Overlooked and Underutilized Sector - Agriculture

Agriculture is the prominent sector of Ethiopia which millions of lives depend on for centuries. The share still stands high compared ...